ሃገር አማን ሰላሳኛ ዕትም

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት(ከ1920 ዓ.ም - 2009 ዓ.ም)
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ታላቅ የታሪክ ምሁርና የኢትዮጵያ ባለውለታ ነበሩ፡፡ በአካለ ሥጋ ካጣናቸው እነሆ ድፍን አምስት አመታት ተቆጠሩ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የካቲት 9/ 2009 ዓ.ም. ነበር ያረፉት፡፡ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሴት አያት ኢምሊን ፖንክረስት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በእንግሊዝ የሴቶችን የመምረጥ መብት የማስከበር ንቅናቄ (UK suffragette movement) የመሩና ለእንግሊዛውያን ሴቶች ፖለቲካዊ ነጻነትን ያቀዳጁ ታላቅ ዓለማቀፋዊ ክብርና ዝናን ያተረፉ የሴት አርበኛ ነበሩ፡፡
በ1928 ዓ.ም. የጣልያን ፋሺስቶች ለ40 ዓመት ሙሉ በበቀል ሲዘጋጁ ኖረው ኢትዮጵያን ሲወርሩ፣ እና በመርዝ ጋዝና የአውሮፕላን ቦምቦች፣ በእሳትና በዘመናዊ ጦር መሣሪያዎች ግማሽ ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በግፍ ሲጨፈጭፉና ብዙው የነጩ ዓለም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለፋሺስቶቹ ዘረኝነት የተሞላበት ወረራ ድጋፉን ሲቸር የሪቻርድ ፓንክረስት እናት Sylvia Pankhurst በእንግሊዝ ምድር ሆና ዓለም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፍና የኢትዮጵያውያንን ጭፍጨፋና ወረራ እንዲያስቆም ሙሉ ጊዜዋን ሰጥታ ስትታገል ነበር፤ የኢትዮጵያ ወዳጅ ጋዜጣ እያሰራጨች፣ ህዝብን በመንገድ ሁሉ እያስቆመች ስትጮህና ስትቀሰቅስ የነበረች ብቸኛ የኢትዮጵያውያን የእውነትና የሀቅ ድምጽ ነበረች፡፡
የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እናት ሲልቪያ ፓንክረስት በዓለማቀፍ ደረጃ ስመጥር የሆነውንና በኢትዮጵያ ላይ የተካሄዱ ብዙ ምሁራዊ ጥናቶችን ያስተባበረውን የኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማህበርን ካቋቋሙ ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ ስለ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ስለ ኢትዮጵያውያን ባህል ብዙ ጽሑፎችን በብዙ ዓለማቀፍ መጽሔቶችና ጆርናሎች ላይ ያሳተመች የኢትዮጵያ የህይወት ዘመን ወዳጅ ነበረች፡፡ መካነ መቃብሯ በሥላሴ ካቴድራል መግቢያው ላይ አርፎ ኢትዮጵያን ለሚወዱ ሁሉ ስለ ሀገር ፍቅር አስታዋሽ ሆኖ ይኖራል፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የእንግሊዝን ሙዝየሞች ደጅ ጠንተው ወደ ሃገራችን ያስመለሱልንን ጥንታዊ ቅርሶች፣ የአክሱም ሃውልትን ከኢጣልያ ለማስመለስ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አብረው የወጡትን የወረዱትን ሁሉ ሳይጨምር ፕሮፌሰሩ በተለያየ መልክ እያገዙ በእግሩ አቁመው ያስኬዱት SOFIES (Society of Friends of Institute of Ethiopian Studies) ብቻ በባለፉት 50 ዓመታት ተግባራቱ ኢትዮጵያን ለራሳችንና ለዓለም በማሳወቅ ያደረገው ተግባር ጉልህ ነው። ፕሮፌሰር ሪቻርድ የምርምር ሥራዎቻቸውና መጽሐፎች በርካታ ናቸው። ፕሮፌሰር ሪቻርድ ለዚች ሀገር ታሪክ ተግተው ሰርተዋልና ሕያው ናቸው።