ሃገር አማን ሃያ ስምንተኛ ዕትም
የዓላማ ጽናት እና ትጋት እንደካትሱ
ሚካያ ግርማ
አንዳንድ ታሪኮች አሉ። ከተዋወቃችኋቸው ዓመታት ቢያልፉም ውስጣችሁ ትኩስ ሆነው የሚያሞቋችሁ። ባለታሪኮቹም አፍ አውጥተው የሚመክሯችሁ። ጃፓናዊው ካትሱ ካይሹ ለእኔ እንደዚያ ነው። በክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል "ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?" መጽሐፍ አማካይነት ይህንን ባለታሪክ ከተዋወቅሁት ከ፲ ዓመታት በላይ ቢቆጠርም ዛሬ ያወቅሁት ያህል ትኩስነቱ በውስጤ ሙቀቱ ይሰማኛል። ታሪኩ አፍ አውጥቶ ያወራኛል። በህይወት ፍትጊያ ነፍሴ ስትታክት ፣ ሥጋዬ ሲደክም "ቻርጅ" ያደርገኝና እንደንሥር አድሶኝ ፣ ጡንቻዬን አፈርጥሞልኝ ያስነሳኛል።
ካትሱ ጃፓን ሁለት መቶ ኀምሳ ዓመታት በሯን ዘግታ ከዓለም ራሷን አግልላ ካለውጭ ጣልቃ ገብነት እንዴት መሰልጠን እንዳለባቸው ትመክር የነበረበት ዘመን ላይ የነበረ ትጉህ ሰው ነው። በወቅቱ በጃፓን ከፈለቁ ታላላቅ ሰዎችም አንዱ ነው። ጃፓናውያን ከዓለም ተነጥለው በሚኖሩበት በዚህ ወቅት ካትሱ በዝና ብቻ ያወቀውን የአውሮፓ ሥልጣኔ ምስጢር ለማወቅ ስለፈለገ ቋንቋቸውን ለመማር ቆርጦ ተነሳ። በዚያን ጊዜ በጃፓን ምድር ያሉ ነጮች ሆላንዶች ብቻ ስለሆኑ የሆላንድን ቋንቋ መማር ግድ ሆነበት። ለመማሪያነት የሚጠቅመውን መዝገበ ቃላት ፈልጎ ሳያገኝ ቀረ። ስለዚህ የመምህሩን መጽሐፍ ተውሶ በእጁ እየጻፈ በሁለት ቅጅ ገለበጠውና አንዱን ለእራሱ አስቀርቶ ሁለተኛውን በውድ ዋጋ ሸጦ ባገኘው ገንዘብ ሌላ መጽሐፍ ገዛበት። በዚህ ብቻ አልተወሰነም።
ስለጦር እቅድ ትምህርት የሚናገር መጽሐፍ ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ ስላላገኘ ለተወሰነ ጊዜ ለማንበብ ብቻ ሲል ያለውን ገንዘብ ሁሉ ከፍሎ ላንድ ዓመት ተከራየውና በእጁ እየጻፈ እንደልማዱ ገለበጠው። በብዙ ድካም ገልብጦ ከጨረሰው በኋላ ጥቂት ጊዜ ቆይቶ ባንድ የመጻሕፍት መደብር ውስጥ ስለጦር እቅድ ጉዳይ የተጻፈ ዳግም አንድ ሌላ መጽሐፍ ድንገት አገኘ። ነገር ግን ለመግዛት ቢጠይቅ ዋጋው ውድ ስለሆነበት ይህን መጽሐፍ ለመግዛት ሲል ከወዳጅ ከዘመድ ገንዘብ እየለመነ ሲያጠራቅም ቆየና ለመግዛት የሚችልበት በቂ ገንዘብ ሲያገኝ ወደመደብሩ ሔደ።
ነገር ግን የሚፈልገው መጽሐፍ ከጥቂት ሰዓታት በፊት አንድ ሌላ ሰው ገዝቶ እንደወሰደው ነገሩት። ካትሱ በዚህ ነገር ተናድዶ ያ ሰው ማን እንደሆነ ነጋዴውን በታጠቀው ሰይፍም ጭምር አስፈራርቶ ይጠይቀዋል። ነጋዴውም ሀብታም የሆነ አንድ የጃፓን መኮንን መሆኑን ስለነገረው ካትሱ ቤቱን እየጠየቀ ከተማውን ሙሉ ከዞረ በኋላ ደረሰበት። ከቤቱም ሰተት ብሎ ገብቶ "ይህን መጽሐፍ በጣም እፈልገዋለሁና ሽጥልኝ" ብሎ ጠየቀው። እንደማይሸጥም ገለጸለት። እንዲያከራየውም ጠየቀው። "አላከራይም" አለው። አውሰኝም ቢል ሊያውሰው እንደማይችል ነገረው። ከብዙ አተካራ በኋላ በስተመጨረሻ በአንድ ነገር ተስማሙ። ካትሱ ማታ ማታ መኮንኑ ቤት እየመጣ መጽሐፉን ሲያነብ እያደረ ጧት ወደቤቱ ለመመለስ። በዚህ አኳኋን ለ፮ ወራት ቆየ። ያን የሚፈልገውን መጽሐፍም አንብቦ ጨርሶ በእጁም አንድ ግልባጭ ጽፎ ወሰደ። መኮንኑም በካትሱ ትጋት እጅጉን ተደንቆ ዋናውን መጽሐፍ እንዲወስደው መረቀለት።
በኋላም ጃፓን የአውሮፓን ሥልጣኔ መቀበል በጀመረች ጊዜ ካትሱ በመረመረው ዕውቀትና በተከታተለው ጥበብ በመርከብና በመድፈኛ ጦር አገሩን ለማገልገል ትልቅ ችሎታ ያለው ሰው ሆኖ ተገኘ። ከዚያም በኋላ ካትሱ ሀገሩን በብዙ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሲያገለግል ኖሯል። በአገልግሎቱም መጀመሪያ አሚራል ፣ ቀጥሎ የመርከብ ሚኒስቴር ፣ ከዚያ የመሳፍንት ምክር ቤት አባል ፣ በመጨረሻ ኮምት ተብሎ ከማዕረግ ወደ ማዕረግ እየተዘዋወረ ከፍ ካለ ትልቅ ደረጃ ከደረሰ በኋላ በ፲፱፻ ዓ.ም በ፸፭ ዓመቱ ሞተ።
#ሀገር አማን ሃያ ስምንተኛ ቅጽ